+251115579202 / 0953222255 / 0953222255Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

በኢትዮጵያ የሙስና ወንጀል ምርመራ ጥራትና ተገቢነትን ማላቅ የሚያስችል ተግባር በጥምረት ለማከናወን ኮሚሽኖቹ ከስምምነት ደረሱ


(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 10/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ተልዕኮ የሆነውን የሙስና ወንጀል መረጃ የማመንጨት እና የምርመራ መዝገብ ዝግጅት ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም ውጤታማነት ላይ የግምገማ መድረክ አካሂደዋል፡፡

በግምገማ መድረኩ የተገኙት የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ፒ.ኤች.ዲ) ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት ከዜጎች የሚቀርቡ የሙስና ወንጀል መረጃዎችን በማመንጨት ተገቢው የሙስና ወንጀል ምርመራ እንዲካሄድባቸው በማድረግ የግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሁም ውጤታማነትን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

እንደሀገር የሙስና ወንጀል መረጃ ቅበላ፣ ምርመራ፣ ክስና ክርክር፣ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በሙስና ወንጀል የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ እና የማስተዳደር ሂደት በላቀ የሙያ ሥነምግባርና ብቃት በግልጽ እንዲከናወኑ በማድረግ ተገማች እና ወጥነት ያለው የሙስና ወንጀል ህግ ማስከበር ሥርዓትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

በዚህም ሁለቱ ኮሚሽኖች፣ የፍትህና የዳኝነት ተቋማት በቅንጅት መረጃና ማስረጃን መሰረት በማድረግ ሙሰኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በበኩላቸው ሁለቱ ኮሚሽኖች በጥምረት መስራት ሙሰኞችን በመረጃና ማስረጃ በማጋለጥ ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረጉም በተጨማሪ የሙስና ወንጀል ምርመራ መዝገብ ዝግጅት ላይ የሚስተዋሉ የህግ ክፍተቶችን በመለየት የሙስና ወንጀልን መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የሙስና ወንጀል በተናጠል ወይም በአንድ ተቋም ብቻ ከመከላከል በጥምረት መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ ለዚህም በመንግስት በኩል ያለው ቁርጠኝነት የቅንጅት ስራን የተሳካ እንደሚያደርገው እና ለውጥ መር ትግል ሊደረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ክቡር ኮሚሽነር ጀነራል አክለውም በበጀት አመቱ 6 ወራት ውስጥ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች በህግ ጥላ ስር ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው ኮሚሽኑ የማስተማር፣ የመከላከል እና ህግ የማስከበር ስራዎችን ከፍትህ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራቱ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።

ሁለቱ ኮሚሽኖች ከዚህ በፊት በሙስና ወንጀል ምርመራ በትብብር ለመስራት የሥራ መግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙት መሠረት የእስካሁኑ ጉዞ እና የቀጣይ የጋራ ሥራን በላቀ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት ለማከናወን በቴክኒክ ኮሚቴ የታገዘ ተጨባጭ ሥራዎች ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

በግምገማ መድረኩ ላይ የሁለቱ ኮሚሽኖች አመራሮች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ትውልድን በሥነምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!

የሙስና ወንጀል መጠቆሚያ አማራጮችን፣ ወቅታዊ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት👇🏾

NCRS ሞባይል መተግበሪያ

ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች

https://play.google.com/store/apps/details…

ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች

https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231

ለሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፦ https://feaccears.gov.et/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/

ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc

ዩትዩብ፡- https://www.youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149

ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

Related Posts