+251115579202 / 0953222255 / 0953222255Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

በመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥና ግልጽነት ላይ በተደረገ ጥናት ውይይት ተካሄደ

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥና ግልጽነት ላይ ያጠናውን ጥናት ለዘርፉ አመራሮች አቅርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ጥናቱ በመንግስት ሆስፒታሎች ለሙስናና ብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ አሰራሮችን በመለየትና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ መንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በሰፊው እየሰራ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ወደ ለውጥ ከመጡ ተቋማት አንዱ ጤናው ዘርፍ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ በንግግራቸው፣ ጥናቱ በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በመለየት የመፍትሔ ሀሳቦችንና የእርምት እርምጃዎችን ለመውሰድ ያግዛል ብለዋል።

የጥናቱ ግኝቶች ለተቋማችን ግብዓቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ብዙ መሰራት ያለባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎቶቻችንን ከሙስና የፀዳ ማድረግ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ጥናት ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮዎች አንዱ የአሰራር ስርዓቶችን በማጥናት ሙስናን መከላከል ነው፤ይህም ጥናት በመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጥ ግልጽነት በመፍጠር ለተቋማት ግኝቶችን ማቅረብና ምክረ ሀሳቦችን መስጠት እንደሆነ ገልጸዋል።

ም/ኮሚሽነሩ አክለውም፣ የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚታግል የሰው ኃይል መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የሰው ልጅ የጤና አገልግሎት ማግኘት መብቱ በመሆኑ የሆስፒታል አገልግሎቶች ከጥቅም ግጭት የፀዱ መሆን አለባቸው፤ ይህንንም አመራሩ በበላይነት መምራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሸኔ ናቸው፡፡

በውይይት ሙስናን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች አንዱ በጥናት የተደገፉ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ የተጠቆመ ሲሆን፣ አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ እንደሚገባም ተመላክቷል። ተሳታፊዎች በውይይቱ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተው በተሰጣቸው ምላሽና ማብራሪያ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የጥናት ሪፖርቱ ለሙስናና ብልሹ አሰራር ያጋልጣሉ ያላቸውን 15 የሚሆኑ ግኝቶች ያመላከተ ሲሆን፣ ለእነዚህም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አሰቀምጧል።

በውይይቱ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባን ጨምሮ የጤና ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በሥሩ ያሉ የትምህርት ጤና ሆስፒታሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ትውለሰድን በሥነምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!

የሙስና ወንጀል መጠቆሚያ አማራጮችን፣ ወቅታዊ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት👇🏾

NCRS ሞባይል መተግበሪያ

ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች

https://play.google.com/store/apps/details…

ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች

https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231

ለሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፦ https://feaccears.gov.et/

ዌብሳይት፦ https://www.feacc.gov.et

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/

ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc

ዩትዩብ፡- https://www.youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149

ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

Related Posts