+251115579202 / 0953222255 / 0953222255Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

የኅብር ቀንን አስመልክቶ በሥራ ቦታ ሥነምግባር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የኅብር ቀንን አስመልክተው በሥራ ቦታ ሥነምግባር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዊ ውይይት አካሂደዋል።

የውይይቱ ዓላማ የኅብር ቀንን አስመልክቶ የኮሚሽኑን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በማነቃቃት፣ ለ2019 በጀት ዓመት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል የሥራ መነሳሳት መፍጠር ነው።

በመድረኩ የኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው፣ የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ህብረ-ብሔርነታቸውን በማጠናከር የሥነምግባር ግንባታ፣ የሙስና ቅድመ-መከላከልና ሕግ ማስከበር ሥራዎችን በውጤታማነት መፈጸም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እነዚህን ተግባራት ውጤታማ ለማድረግም መልካም ሥነምግባርን መላበስ እንደሚያስፈልግ አቶ እሸቴ አስገንዝበዋል።

በኮሚሽኑ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትም የውስጥ ኦዲት፣ የሕግ አገልግሎት፣ የተቋማዊ ለውጥ እና የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ሥራ ክፍሎች በእቅዳቸው አካተው በቀጣይ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የኮሚሽኑ የሥነምግባር ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው፣ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ለሥራቸው ታማኝ በመሆን የተሰጣቸውን ተግባር ሥነምግባራዊነትን በመላበስ መፈጸም እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በቀጣይም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማረምና የሥራ ቦታ ሥነምግባርን በማሻሻል የተሰጣቸውን ተልዕኮ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ በሥራ ቦታ ሥነምግባር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በኮሚሽኑ የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ሥልጠና መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኃላሸት ደሳለኝ ተሰጥቷል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በሥራ ቦታ ሥነምግባር ዙሪያ ጥያቄዎችን፣ ሀሳቦችንና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። የመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይም በተሳታፊዎች የጋራ ውይይትና ስምምነት የተደረሰባቸውን የኮሚሽኑን ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ ለማስፈጸም የሚያግዙ ስድስት ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ ቀርቧል።

Related Posts