+251115579202 / 0953222255 / 0953222255Kazanchiz Addis Ababa, Ethiopia

የ325 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ የተቀበሉት ባለሥልጣን ሞት ተፈረደባቸው



(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሐምሌ 01/2018 ዓ.ም) በምስራቃዊ ቻይና የሚገኝ ፍርድ ቤት በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ 2.2 ቢሊዮን ዩዋን በላይ ወይም 325 ሚሊዮን ዶላር በሙስና በመቀበል የተከሰሱት የቀድሞ የከተማዋ አስተዳደር ባለሥልጣን ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

ቅጣቱ የተላለፈባቸው ያንግ ዩሊን ከአውሮፓውያኑ 1993 እስከ 2023 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በናንጂንግ ከተማ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል ተብሏል።

የቀድሞው ባለሥልጣን በማጭበርበር፣ ሥልጣንን አላግባብ በመጠቀም እና ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀሎች ተከስሰዋል። በእነዚህ ድርጊቶች አግኝተዋል የተባለው የገንዘብ መጠን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቀረቡ ክሶች ያልታየ መሆኑ ተጠቁሟል።

የ69 ዓመቱ የቀድሞ ባለሥልጣን ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው ሌሎች የኢንጂነሪንግ ውሎችን፣ የመሬት ባለቤትነት ዝውውር እና ገንዘብ እንዲያገኙ ማድረጋቸው ተገልጿል። ለዚህም በምላሹ ገንዘብ እና ቁሶችን መቀበላቸው ተዘግቧል።

ያንግ ምርመራ የተከፈተባቸው፤ ፕሬዝዳንት ዢ ሺፒንግ በከፈቱት የፀረ-ሙስና ዘመቻ መሆኑ ተመላክቷል። ይህ ዘመቻ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች፣ ትልቅ ባንኮች እና ሌሎች ዘርፎችንም መንካቱ ተጠቁሟል።

ዢ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት የፀረ-ሙስና ዘመቻዎችን ከፍተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ዘመቻዎች የፖለቲካ ተቀናቃኞችን ለማጥቃት ውለዋል የሚል ክስ ይቀርብባቸዋል ተብሏል።

ከዚህ በፊት 1.1 ቢሊዮን ዩዋን በሙስና ተቀብለዋል የተባሉ አንድ ባለሥልጣን 2021 ላይ በሞት መቀጣታቸውን አስታውሶ ቢቢሲ አማረኛ ዘግቧል።

Related Posts