ክልሉ የሙስና መከላከል ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የ2018 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሙስና መከላከል ሥራዎች አፈፃፀም ሪፖርት በዝርዝር ገምግሟል።

ኮሚሽኑ በሩብ ዓመቱ 103 የተለያዩ የሙስና ጥቆማዎችን የተቀበለ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥ 45 የሙስና ጥቆማዎችን በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ 3 ሚሊዮን 283 ሺህ 679 ብር ከብክነት ማዳኑን ጠቅሷል።

16 የሙስና ጥቆማዎች በአስተዳደራዊ እርምጃ መፈታታቸውን፣ በ19ኙ ላይ የምክር አገልግሎት መሰጠቱን፣ ስምንት ጥቆማዎች ለፍትህ ቢሮ መተላለፋቸውን እንዲሁም በ15ቱ ላይ የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።

በከተማና ገጠር አከባቢዎች ሀሰተኛ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ጋር ተያይዞ የሚደረሱ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል ዘርፈብዙ ተግባራት የተከናወነ ሲሆን፣ 2 ሺህ 585 ካሬ ሜትር በከተማና 0.25 ሄክታር የገጠር መሬት ከምዝበራ ማዳን የተቻለ መሆኑን ከክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ጋር በተያያዘ በሩብ ዓመቱ 697 አዲስ ሠራተኞች ሀብታቸውን ያስመዘገቡ ሲሆን፥ ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑ 26 የመንግሥት ሠራተኞች እያንዳንዳቸው ከአንድ ሺህ ብር ቅጣት ጋር ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉ ተገልጿል።

ዜጎች ማንኛውንም አገልግሎቶች ከተቋማት ለማግኘት በሚያደርጉት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያጋጥማቸውን ሙስና እና ብልሹ አሠራር በቁርጠኝነት በማጋለጥ ለፀረ-ሙስና ትግል ሚናቸውን እንዲወጡ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ሙሉሰዉ ዘዉዴ ጥሪ አቅርበዋል።

ከሙስና የፀዳች እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን እናድርግ!

NCRS ሞባይል መተግበሪያ

ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች

https://play.google.com/store/apps/details

ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች

https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231

Related Posts