ኮሚሽኑ በፌደራል ተቋማት የንብረት አያያዝና አወጋገድ አሰራር ሥርዓት ግልጽነት ላይ ያካሄደውን ጥናት ለገንዘብ ዘርፍ ከፍተኛ አመራሮች አቀረበ


(ፌ.ሥ.ፀ.ሙ.ኮ ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም አዲስ አበባ) የፌደራል የሥነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በፌደራል ተቋማት የንብረት አያያዝና አወጋገድ አሰራር ሥርዓት ግልጽነት ላይ ያጠናውን ጥናት ለገንዘብ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች አቅርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት በኮሚሽኑ የሙስና መከላከል ጥናት ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው ኮሚሽኑ በትውልድ ሥነምግባር ግንባታ፣ በሙስና ቅድመ መከላከልና ህግ ማስከበር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

ከዚህ አንፃር በበጀት አመቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዘርፍ ተኮር ጥናት በማካሄድ ለተቋማቱ ምክረ ሀሳብ እያቀረብን የሪፎርማቸው አካል በማድረግ ለውጥ እያመጡበት ነው ብለዋል።

ም/ኮሚሽነሩ አክለውም በሙስና የሚሳተፋ ግለሰቦችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ከፌደራል ፖሊስና ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ጥናቱ ተቋማት በቂ ንብረት እያላቸው መግዛት፣ የንብረት ቆጠራ በየጊዜው አለማድረግ፣ ህጋዊ አሰራሮችን ሳይከተሉ ንብረት ማስወገድ እና በግዥ የሚቀርቡ እቃዎች ላይ ተገቢ ቁጥጥር አለማድረግ የሚሉ ክፍተቶችን ስለሚያመላክት ችግሩን ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት በማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል።

የተቋማት አመራሮችም ሙስናን ለመታገል በቅንጅት ከመስራት ባለፈ በባለቤትነት መምራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፍቃዱ ሆረታ በበኩላቸው የጥናቱ ግኝቶች በቀጣይ ለምንሰራቸው አጋዥ ይሆናሉ፤ ችግሩን ለመቅረፍም በርካታ ተግባራት እየተሰሩ ቢሆንም ሙስናን ጨርሶ ማስወገድ አልቻልንም ብለዋል።

ሙስናን ለመከላከል አመለካከት ላይ መስራት ይኖርብናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ችግር ፈጥረው የተገኙትን ተጠያቂ ለማድረግ ተቋማችንን በጥልቀት በማየት ሌቦችን ማጋለጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም መንግስት በሙስና ድርጊት የሚሳተፋ ግለሰቦችን ተጠያቂ የማድረግ ሥራን ማስቀጠል አለበት። በዘርፍ  ደረጃም አሰራሮችን በማዘመንና ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ አለብን ብለዋል።

የኮሚሽኑ ሙስና መከላከል ጥናት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገዛኸኝ ጋሻው በበኩላቸው ጥናቱ በፌደራል ተቋማት የንብረት አያያዝና አወጋገድ ለሙስና እና ብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ አሰራሮችን በመለየትና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥናቱ ሪፖርት ለሙስናና ብልሹ አሰራር ያጋልጣሉ ያላቸውን 11 የሚሆኑ ግኝቶች ያመላከተ መሆኑን ገልፀው፣ ለእነዚህም የመፍትሔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል ብለዋል።

በጥናቱ ከታዩና ከተለዩት ክፍተቶች መካከል ለአብነት አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በወቅቱ አለመወገድ፣ መጠቀሚያ ግዜያቸው ያለፈ ኬሚካሎች በወቅቱ አለመወገድ፣ የሚወገዱ ንብረቶች አቀማመጥ በንብረቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ፣ ህጋዊ አሰራርን ሳይከተል ንብረት መወገዱ፣ የሚወገዱ ንብረቶች መረጃ በአግባቡ ተደራጅቶ አለመያዝና አዲስ ከሆኑት ጋር ተቀላቅለው መያዛቸው እንዲሁም በግዥ የሚቀርቡ ዕቃዎች ላይ ተገቢ ቁጥጥር የማይደረግ መሆኑ የሚሉት ተመላክተዋል።

እንዲሁም አገልግሎት የማይሰጡ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በወቅቱ አለመወገድ፣ የሚወገዱ ንብረቶችን ለማስወገድ የሚወጣ የጨረታ ሂደት ተደራሽና አሳታፊ አለመሆን፣ በንብረት አወጋገድ ላይ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር አለመጠናከር እና የንብረት አስተዳደር መመሪያ በአግባቡ አለመተግበሩ በጥናቱ ከተስተዋሉ ግኝቶች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስቴርና በስሩ ተጠሪ የሆኑት የመንግስት ግዥ አገልግሎት፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ፣ እዳና ሀብት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፥ የተለያዩ ሀሳቦችን አንስተው በተሰጣቸው ምላሽና ማብራሪያ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

ትውልድን በሥነምግባር፤ ተቋምን በአሰራር!

የሙስና ወንጀል መጠቆሚያ አማራጮችን፣ ወቅታዊ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት👇🏾

NCRS ሞባይል መተግበሪያ

ለAndroid ስልክ ተጠቃሚዎች

https://play.google.com/store/apps/details…

ለApple or iPhone ስልክ ተጠቃሚዎች

https://apps.apple.com/us/app/ncrs/id659366231

ለሀብት ማሳወቅና ምዝገባ፦ https://feaccears.gov.et/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/feaccOfficial/

ቴሌግራም፦ https://t.me/feacc

ዩትዩብ፡- https://www.youtube.com/@federalethicsanti-corrupti149

ትዊተር፦ https://twitter.com/EthiopiaFeacc በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

Related Posts