የፀረ-ሙስና ትግሉ የህዝብና የመንግሥት ቋሚ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት – ምክትል አፈ ጉባዔ የተከበሩ ሎሚ በዶ

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሃ-ግብር በዛሬው ዕለት በድምቀት አክብሯል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ ሎሚ በዶ ዛሬ የምናከብረው የፀረ-ሙስና ትግል ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ያለንበትን ለመገምገምና ወደፊት የምንመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን የሚያስችለን ነው ብለዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዋና መወያያ ነጥቦች መካከል ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠ አጀንዳ መሆኑን አንስተው፤ የፀረ-ሙስና ትግሉ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ የጋራ ሀገራዊ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፉት 25 ዓመታት ኮሚሽኑ በሶስት ዋና ዋና የትግል አዕማድ ላይ ተመስርቶ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ያስታወሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፤ የዜጎችን አስተሳሰብ የሚቀርፅ የሥነምግባር ግንባታ፣ የሌብነት ቀዳዳዎችን የሚደፍን የሙስና ቅድመ-መከላከል እና ጥፋተኞችን ለፍትህ የሚያቀርብ የህግ ማስከበር ስራዎች ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ሶስት መሰረቶች የፀረ-ሙስና ትግሉ የማዕዘን ድንጋዮች ሆነው አሁንም ያገለግላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ በ25 ዓመታት የሥራ ጉዞው በሥነ-ምግባር ግንባታ፣ በሙስና መከላከል፣ የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግ፣ በተቋማት የፀረ-ሙስና አቅም ማጠናከርና በተጠያቂነት ስርዓት ዝርጋታ ከሁሉ በላይ ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት መንግስት ሙስናን ለመታገል ዘመናዊ እና መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎችን በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በተለይም ሀገራዊ የጥቆማ መቀበያ ስርዓት፣ የዜጎችን ድምፅ ያለስጋት እንዲሰማ አድርጓል ብለዋል።

ሙስና የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግባር፣ የሞራል፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የልማት፣ የሀገር እና የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በመሆኑ ሁሌም ቋሚ የህዝብና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ወይዘሮ ሎሚ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የተገኙት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ እውነቴ አለነ፤ መንግስት የፈጠራቸውን መልካም እድሎች በመጠቀም ለሀገር ልማት በጋራ መትጋትና ብልሹ አሰራሮችንም መታገል ይገባል ብለዋል።

የሙስና ትግል የመጀመሪያ ምዕራፍ መከላከልን፣ ምርመራንና ክስን በአንድ ተቋም በማድረግ ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል። ሆኖም እንቅስቃሴው ህዝብን የትግሉ ባለቤት ያላደረገ፣ የሙስና መከላከል ስራን የረሳና ለትውልድ የሥነ-ምግባር ግንባታ ቦታ የማይሰጥ ነበር ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ከሚሊኒየሙ መባቻ ጀምሮ ለውጡ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ የነበረው ወቅት በልማታዊ መንግስት ስም ከፍተኛ ጣልቃገብነት የተካሄደበት እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት እንደነበር አንስተዋል።

በዚህም ምክንያት የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ሜጋ የመንግስት ፕሮጀክቶች በሙስና እና በሌብነት ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር አስተዋል።

በሶስተኛው ምዕራፍ፣ ከሀገራዊ ለውጡ መባቻ ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ከሙስና ትግል አኳያ መሰረታዊ ለውጥ መደረጉን ገልጸዋል።

በኮሚሽኑ ላይ ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል ዋነኛው የህግ ሪፎርም መሆኑን አንስተው፤ ሙስናን በአንድ ተቋም ብቻ መታገል ስለማይቻል ሁሉም የመንግስት ተቋማት የትግሉ ባለቤት እንዲሆኑ መደረጉን አንስተዋል።

የዲጂታላይዜሽንን መልካም እድሎች በመጠቀም አገልግሎቶችን ከሰው ንክኪ ነፃ እና አካታች በሆነ መንገድ ማቅረብ መቻሉ፣ መሰረታዊ የእሳቤ ለውጥ ማምጣቱንና ለፀረ-ሙስና ትግሉ ጠንካራ መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በእነዚህ አዎንታዊ ለውጦች እና የመደመር እሳቤ በፈጠራቸው አዳዲስ እድሎች በመጠቀም፣ በአሁኑ ወቅት ሙስና ጎልቶ በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ ያተኮረ ዘመቻ መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል።

በመሆኑም የተጀመሩ አዎንታዊ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ በመጪው ጊዜም ያልተቋረጠና የተቀናጀ የሙስና ትግል ማድረግ እንደሚገባ አቶ እውነቴ አሳስበዋል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ኮሚሽኑ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመታገል የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመነደፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

25ኛ ዓመታችንን ስናከብርም ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን ነቅሰን በማውጣት በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ዝግጁነታችንን እያረጋገጥን ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመፍታት፣ ተጠያቂነትን በማስፈንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ተግባራት ለማሳለጥ በሚያስችል ጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተለይም ከሀብት ምዝገባ አንጻር አዎንታዊ ለውጦች መኖራቸውን ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሀብታቸውን ባላስመዘገቡ አካላት ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የፌዴራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው ከሚሽኑ ባለፉት አመታት በትውልድ ሥነምግባር ግንባታ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልፀው፤ በቀጣይም አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመው፤ በሚቀጥለውም ዓመትም ለአዳዲስ የፖርላማ አባላትን ለማሰልጠን እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ኮሚሽኑ በ25 ዓመቱ የፀረ-ሙስና ትግሉ ትናንት፣ ዛሬ እና ነገን ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ እና ዶክመተሪ ፕሮግራም ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በመርሃ ግብሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም አበላት፣ በፌደራል፣ በክልል እና ከተማ አስተዳደር የሥነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያገለገሉ የቀድሞ ኮሚሽነሮች፣ በኮሚሽኑ ከ20 ዓመት በላይ ላገለገሉ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

Related Posts